ይህ ውል በውል ስም በ"ዕቁብ ቤት ኃ/የተ/የግል/ማህበር" ከዚህ በኋላ ("ዕቁብ ቤት") በመባል በሚጠራው እና በውል ተቀባይ "የዕቁብ ቤት አባል ለመሆን በሚሳተፈው ዕቁብተኛ" ከዚህ በኋላ ("ዕቁብተኛ") በመባል በሚጠራው መካከል በዛሬው ዕለት ተፈጽሟል።
አንቀጽ 1.የውሉ ዓላማ
ይህ የውል ስምምነት ዕቁብ ቤት ተብሎ የሚጠራው ኃ/የተ/የግል/ማህበር ለዕቁብተኛው በኤሌክትሮኒክስ በታገዘ ሁኔታ አዋጅ ቁጥር 1205/2012 በሚፈቅደው አግባብ ዕቁብ ለመጣል የሚፈልጉ ዕቁብተኞችን በአባልነት በመመዝገብ እና ግዴታቸውን እንዲወጡ በማድረግ የኤሌክትሮኒክስ ንግድን ለማስፋፋት፣ ዕቁብተኞች ኢኮኖሚ አቅማቸው እንዲዳብር ለማሰብ በዕቁብ ቤት እና የዕቁብ አባል ለመሆን በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ ዕቁብ ለመጣል ኢኮኖሚያቸው እንዲዳብር ፍላጎት ባላቸው እና የዕቁብ አባል ለመሆን ፈቃደኛ በሆኑት በዕቁብ ቤት እና በዕቁብተኛው መካከል ዕቁብ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅበት ድረስ የሚኖራቸው መስተጋብር ምን መሆን አለበት የሚለውን ለመደነገግ በዕቁብ ቤት እና በዕቁብተኛው መካከል ይህ ውል ተፈጽሟል።
አንቀጽ 2.የዕቁብ አባልነት መስፈርት እና የዕቁቡ አጀማመር
አንድ ዕቁብተኛ የዕቁቡ አባል ለመሆን በሕጋዊ ሥራ ላይ የተሰማራ እና/ወይም ለዕቁብ መዋጮ የሚሆን በቂ ገቢ ያለው።
በተጨማሪያም ግለሰቡ በዚህ ውል ደንብና ሁኔታዎች ለመገዛት እና ዕቁብ ቤት በየጊዜው የሚጠይቃቸውን ሌሎች መስፈርቶች በአግባቡ ለማሟላት ፈቃደኛ መሆን ይኖርበታል።
ዕቁብተኛው የዕቁቡ አባል ለመሆን በኤሌክትሮኒክስ በታገዘ ሁኔታ ውሉን ካነበቡ በኋላ የዕቁቡ አባል ለመሆን ፈቃደኛ መሆናቸውን ለመግለጽ "ይስማማሉ" የሚለውን በመጫን የውሉን ደንቦች እና ሁኔታዎች የተቀበሉ መሆናቸውን ማረጋገጫ በመስጠት የዕቁቡ አባል ይሆናሉ።
ዕቁቡ ጥቅምት 16 ፤ 2019 የሚጀምር ሲሆን በትክክለኛው ለ 105 ቀናት የሚጣል ይሆናል። በዚህ አንቀጽ አፈጻጸም ሲባል እሁድ እንደ ወር አይቆጠርም።
አንቀጽ 3.የውል ተፈጻሚነት
ዕቁብተኛው በላይ በአንቀጽ 2 በተጠቀሰው አግባብ የዕቁቡ አባል ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ ዕቁቡ እስኪጠናቀቅ እና ዕቁብተኛው በዚህ ውል አግባብ ግዴታቸውን እስኪወጡ ድረስ ውሉ ተፈጻሚ ይሆናል። በተጨማሪም ዕቁቡ ከተጀመረበት ቀን አንስቶ ቅዳሜ እና እሁድ ጨምሮ በትክክለኛው ለ 105 ቀናት የሚጣል ይሆናል።
ይህ ዕቁብ 105 ዕቁብተኛ አባላት ይኖሩታል፤ ዕቁቡ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ በሁሉም የዕቁቡ አባል ላይ ተፈጻሚ ይሆናል።
አንቀጽ 4.የዕቁብ አማራጭ ሁኔታ እና የአገልግሎት ክፍያ
በዚህ ውል የዕቁብ ቤት አባል የሆነ ዕቁብተኛ አባል ከሆነበት ቀን ጀምሮ በቀን 5000.00 (አምስት ሺህ ብር) ይጥላል።
ዕቁብተኛው ዕቁቡ ለሁሉም ዕቁብተኞች ደርሶ እስኪጠናቀቅ ድረስ ለተከታታይ 105 ቀናት በቀን ብር 5000.00 (አምስት ሺህ ብር) የሚጣል ይሆናል።
አንቀጽ 5.የዕቁብ አወጣጥ ሁኔታ
ይህ ዕቁብ ከተጀመረበት ቀን ጀምሮ ለ 105 (አንድ መቶ አምስት) ቀን የሚጣል ይሆናል። ዕጣው የሚወጣውም የኤሌክትሮኒክስ ዘዴ በመጠቀም ይሆናል።
ዕቁብተኞች ከሰኞ እስከ እሁድ ለሰባት ተከታታይ ቀናት ለጣሉት የዕቁብ መዋጮ ሰባት ዕጣዎች በየሳምንቱ ሰኞ ዕለት ከቀኑ 10:00 ሰዓት ላይ በዕቁብ ቤት የሞባይል መተግበሪያ የቀጥታ የዕጣ አወጣጥ ስርዓት የሚወጡ ይሆናል። ይህ ሂደት ዕቁቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚቀጥል ሲሆን ዕቁብተኛውም ሂደቱን በሞባይል ስልካቸው በቀጥታ መከታተል ይችላል።
የዕቁብ ዕጣ በሚወጣበት ዕለት ከሰባት ቀናት በላይ የዕቁብ መዋጮ ክፍያ ውዝፍ ያለበት ማንኛውም ዕቁብተኛ በራሱ ፈቃድ ዕቁቡን እንደቆረጠ የሚቆጠር በመሆኑ ዕጣ የወጣለት የዕቁብ ገንዘብ እንዲሰጠው መጠየቅ አይችልም። በመሆኑም ዕቁብተኛው ዕቁቡን ሲቀላቀል በገባው የዕቁብ ቤት የአባልነት ስምምነት መሠረት ዕቁቡን እስካቆመበት ጊዜ ድረስ የዋጣው የዕቁብ መዋጮ ገንዘብ ተመላሽ የሚደረግለት ዕቁቡ ሲጠናቀቅ ብቻ ነው።
ዕቁብተኞች መክፈል ያለባቸው የሰባት ቀን የዕቁብ መዋጮ ክፍያ ወይም በዕለታዊ ክፍያ ከሰኞ እስከ እሁድ ባለው ጊዜ ውስጥ ከሰኞ 10:00 ሰዓት በፊት መክፈል ይኖርባቸዋል።
ዕጣ ውስጥ መሳተፍ የሚችሉ ዕቁብተኞች ከሰባት ቀናት በላይ ያልተከፈለ ውዝፍ የዕቁብ መዋጮ ክፍያ የሌለባቸው ከሆነ ብቻ ነው፤ ውዝፍ ያለባቸው ከሆነ ዕጣ ውስጥ ሊሳተፉ አይችሉም።
እጣው ሲወጣ ለአንድ ዕቁብተኛ የሚደርሰው የገንዘብ መጠን 500,000 (አምስት መቶ ሺህ ብር) ይሆናል።
የዕቁቡ ዕጣ ሲወጣ ዕጣ የወጣለት ዕቁብተኛ ዕቁብ ደርሶት ከሚሰጠው 525,000.00 (አምስት መቶ ሃያ አምስት ሺህ ብር) ብር ውስጥ 25,000.00 (ሀያ አምስት ሺህ ብር) የአገልግሎት ክፍያ ተቀንሶ ይሰጠዋል።
ከላይ በአንቀጽ 5.7 አግባብ ዕቁብ ከደረሰው ዕቁብተኛ የተቀነሰው የአገልግሎት ክፍያ ወደ ዕቁብ ቤት ገቢ የሚሆን ይሆናል።
ዕቁብተኛው የዕቁብ ዕጣ ሲወጣለት በዚህ ውል መሠረት የሚጠበቅባቸውን ቅድመ ሁኔታ በማሟላት እና ከዕቁብ ቤት ጋር በቅድሚያ የውል ስምምነት በመፈጸም ዕጣ የወጣላቸው የዕቁብ ገንዘብ ከሚሰበሰብበት የባንክ ሒሳብ በፋይናንስ ተቋማት በኩል የሚሰጣቸው ይሆናል።
አንቀጽ 6.የዕቁብ ዕጣ የወጣለት ዕቁብተኛ የዕቁብ ገንዘብ ለመቀበል ማሟላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች
ዕጣ የወጣለት ዕቁብተኛ፦
- የታደሰ የአዲስ አበባ ከተማ የነዋሪነት መታወቂያ ወይም የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ቁጥር (በተጨማሪነት ፓስፖርት እና መንጃ ፈቃድ)፤ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ፤ የትዳር ሁኔታውን የሚያሳይ ማስረጃ፤ ግብር ከፋይነት መለያ ቁጥር (TIN) ሠርተፊኬት፤
- ዕቁቡን የሚቀላቀልበት ስልክ ቁጥር በስሙ የወጣ የራሱ ስልክ ቁጥር ወይም በቀጣይ የሚገለገልበት ስልክ ቁጥር የሆነ፤
አንቀጽ 7.የዕቁብ ዕጣ ወጥቶለት ገንዘብ የወሰደ ዕቁብተኛ ግዴታዎች
ዕጣ የወጣለትን የዕቁብ ገንዘብ በሚወስድበት ጊዜ ቀሪ የዕቁብ መዋጮ ክፍያዎችን ሳይዘገይና ሳያቋርጥ እንደሚከፍል ለማረጋገጥ የሚያስችል እና ዕቁብ የደረሰውን ገንዘብ የሚያንስ ዋጋ የሌለው እና ዕቁብ በኩል ተቀባይነት ያለውን መያዣ ይኸውም፦
- የራሱን ቼክ ወይም
- በመያዣነት ለመስጠት ፈቃደኛ የሆነ ሌላ ሰው ቼክ፤
- የመኪና የባለቤትነት ማረጋገጫ ሊብሬ ወይም
- የማይነቃነቅ ንብረቶችን በመያዣነት ማቅረብ የሚችል፤
ዕቁብተኛው በአንቀጽ 5 መሠረት የዕቁብ ዕጣ ሲወጣለት በዚህ ውል መሠረት የሚጠበቅባቸውን ቅድመ ሁኔታ በማሟላት እና ከዕቁብ ቤት ኃ/የተ/የግል/ማህበር ጋር በቅድሚያ የውል ስምምነት በመፈጸም ዕጣ የወጣላቸው የዕቁብ ገንዘብ መደበኛ የዕቁብ መዋጮ ገንዘብ ከሚሰበሰብበት ማዕከላዊ የባንክ ሒሳብ በፋይናንስ ተቋማት በኩል የሚሰጣቸው ይሆናል።
አንቀጽ 8.የዕቁብ ዕጣ ማስተላለፍ
ዕቁብ የወጣለት ዕቁብተኛ ዕጣውን ለሌላ ዕቁብተኛ ማስተላለፍ ሲፈልግ በዕቁብ ቤት ኃ/የተ/የግል/ማህበር በሚዘጋጀው የመጠየቂያ ፎርም ላይ በመሙላት ከማህበሩ ፈቃድ ሲያገኝ የወጣለትን የዕቁብ ዕጣ ማስተላለፍ ይችላል። ፈቃድ አሰጣጡን እና ዝርዝር ሁኔታውን በተመለከተ ከዕቁብ ቤት ኃ/የተ/የግል/ማህበር ጋር በሚፈራረሙት ውል ላይ በሚገለጸው አግባብ የሚፈጸም ይሆናል።
አንቀጽ 9.የዕቁብተኛው ኃላፊነት እና ግዴታ
ሌሎች የዚህ ውል ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ሆነው ዕቁብተኛው የሚከተሉት ግዴታዎች አለባቸው፤
የዕቁብ መዋጮ ክፍያዎችን ሳይዘገዩ እና ሳያቋርጡ በዚህ ውል ድንጋጌዎች መሠረት የመክፈል ግዴታ አለበት።
የዕቁብ እና ሌሎች ክፍያዎችን በዕቁብ ቤት ኃ/የተ/የግል/ማህበር በሚፈቀደው አግባብ በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ አማራጮች በመጠቀም መክፈል ይኖርበታል።
አንቀጽ 10."ዕቁብ ቤት" ኃላፊነት እና ግዴታ
አዋጅ ቁጥር 1205/2012 በሚደነግገው አግባብ ኃላፊነቱን ህጉ በሚፈቅደው አግባብ መወጣት፤
የዕቁብተኞችን ምስጢር መጠበቅ በተለይም በሕግ ግዴታ ከተጣለባቸው ጉዳዮች ውጭ ከዕቁብተኞች ፈቃድ ውጭ ስለ ዕቁብተኞች መረጃ ለሦስተኛ ወገን አለመስጠት፤
ዕቁቡን በተመለከተ የሚወጡ አዳዲስ አሰራሮችን ለዕቁብተኞች ቀድሞ መረጃ እንዲደርሳቸው ማድረግ፤
በዚህ ውል የተጠቀሱ እና ተጨማሪ ስምምነት ከዕቁብተኞች ጋር መፈራረም በሚያስፈልጉ ጉዳዮች ላይ እንደአስፈላጊነቱ ቅጾችን በማዘጋጀት ከአባላቱ ጋር ውል በማድረግ ግልጽነት እና ተጠያቂነት ያለው አሰራር መዘርጋት፤
የሞባይል መተግበሪያውን በባለቤትነት ይይዛል፤ ይቆጣጠራል፤ ያስተዳድራል፤ እንዲሁም ማንኛውም ችግር ቢጋጥም መፍትሔ ይሰጣል፤
ከዕቁብ ጋር በተያያዘ መደበኛ የዕቁብ መዋጮ ክፍያ በጥሬ ገንዘብም ሆነ በሌላ የክፍያ አማራጭ ከዕቁብተኞች አይቀበልም፤
የዕቁብ ክፍያ ያዘገዩ ወይም ዕጣ ከወጣላቸው በኋላ ዕቁቡን ያቋረጡ ዕቁብተኞች በዚህ ውል መሠረት ሕጋዊ ወለድ፣ ቅጣት እና ወጪ ጋር እንዲመልሱ ክስ ማቅረብን ጨምሮ ሌሎች አግባብነት ያላቸው ሕጋዊ እርምጃዎች ይወሰዳሉ፤ እንዲሁም ዕቁብተኛው ያያዘዘውን መያዣ ወይም ዋስትና በመጠቀም ገንዘቦችን ተመላሽ ያደርጋል፤
ዕቁብተኛው ከዕቁብ ጋር በተያያዘ በወንጀል ድርጊት ውስጥ ስለመሳተፉ በቂ ማስረጃ/መረጃ ሲኖረው ጉዳዩን ለሚመለከተው የመንግሥት አካል ያሳውቃል።
በተለያዩ መንገድ ያገኛቸውን እና ዕቁብተኞችን የሚመለከቱ ሚስጥራዊ መረጃዎች ሚስጥራዊነታቸው ተጠብቆ ይይዛል። በሕግ ስልጣን ለተሰጠው አካል ወይም ይህን ውል ለማስፈጸም ካልሆነ በቀር ሚስጥራዊነቱ የተጠበቀ ነው።
ዕጣ ወጥቶልኛል በሚል የሚመጡ ሰዎችን ትክክለኛ ማንነት ለማጣራት አስፈላጊውን ጥረት ያደርጋል፤ የሰዎቹን ትክክለኛ ማንነት በበቂ ሁኔታ ማጣራት ካልተቻለ ደግሞ የዕቁብ ገንዘብ እንዳይከፈላቸው የማድረግ ኃላፊነት አለበት። በተጨማሪም ለማታለል በማሰብ የተለያዩ ስልክ እና ማንነት ተጠቅመው ከአንድ ዕቁብ በላይ አቁበው የሚገኙ ሰዎች ሲያጋጥሙ በዚህ መንገድ የተከፈቱ ዕቁቦችን ያግዳል።
አንቀጽ 11.አለመግባባቶች የሚፈቱበት አግባብ በተመለከተ
የዚህን ውል ዓላማ ማሳካት እንዲቻል በተዋዋይ ወገኖች መካከል የሚፈጠር አለመግባባት በሁለቱ ወገኖች መካከል በመነጋገር እንዲፈታ ተዋዋዮች የሚችሉትን ጥረት ያደርጋሉ። ሆኖም ከተዋዋይ ወገኖች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶች በንግግር መፍትሔ ማግኘት የማይቻል ከሆነ ጉዳዩን ወደ ግልግል ዳኝነት በመውሰድ አለመግባባቱ እንዲፈታ የሚደረግ ይሆናል።
አንቀጽ 12.ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች
ዕቁብ ቤት የዚህን ውል ደንብና ሁኔታዎች ለዕቁብተኞች በቅድሚያ በማሳወቅ በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ ሊያሻሽል ይችላል።
ይህ ስምምነት የማይሸፍናቸው ጉዳዮች አግባብነት ባላቸው የኢትዮጵያ ሕጎች መሠረት የሚሸፈኑ ይሆናል።
በዚህ ውል ውስጥ በወንድ ጾታ የተገለጸው አገላለጽ በተመሳሳይ መልኩ ለሴትም ጾታ ያገለግላል። በሴትም ጾታ የተገለጸውም በተመሳሳይ መልኩ ለወንድ ጾታም ያገለግላል።
በመጨረሻም አግባብነት ባላቸው የሀገሪቱ ሕጎች፣ በዚህ ውል እና ዕቁብ ቤት ባለው አሰራር መሠረት የሚጣሉባቸውን ሌሎች ግዴታዎችና ኃላፊነቶች በአግባቡ መወጣት አለባቸው።